Fana: At a Speed of Life!

ቻይና በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በዲጂታላይዜሽን እና ዘመናዊ አሰራሮች ላይ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡

የሁለቱን ሀገራት የረጅም ጊዜ የጠነከረ ግንኙነት በዘመናዊ አመራር ደረጃ ለማረጋገጥ ታሳቢ ያደረገ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም በሁለቱ ሀገራት መካከል የተሻለ ግንኙነትን በዘመነ መንገድ ለማዳበር የጋራ ልምዶችን መጋራት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቻይና የልማት ልምዷን ከምታጋራቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች እና በዚህ ላይም በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በዲጂታላይዜሽን እና ዘመናዊ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን በቻይና አፍሪካ ጉባኤ ላይ ዢ ጂምፒንግ መናገራቸውንም የቻይና ምክትል ትምህርት ሚኒስትሩ ው ያን በመድረኩ አንስተዋል።

ምክትል ሚኒስትሩ አክለውም በቻይና አፍሪካ ትብብሮች ውስጥ የትምህርት ዘርፉን ማሻሻልም አንዱ እና ዋናው የትኩረት አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣዮቹ ዓመታትም በአህጉሪቱ በዚሁ ዙሪያ ዲጂታላይዜሽንን በማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው÷ ሀገራቱ ካላቸው የረጅም ጊዜያት የትብብር ግንኙነት በመነሳት የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እና የትምህርት እድል በመስጠት የቻይና ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.