Fana: At a Speed of Life!

በመርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ የደረሰውን የእሳት አደጋ መንስኤ እየመረመረ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንትና ምሽት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሸማ ተራ ነባር የገበያ ማዕከልና በአካባቢው ባጋጠመ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

አደጋውን ለመከላከልና በአደጋው ምክንያት ሌላ ወንጀል እንዳይፈፀም እንዲሁም የአደጋ ተከላከይ ሠራተኞች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሠላምና ፀጥታ መዋቅር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች ተቋማትም ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አደጋው እንዳይባባስ ከፍተኛ ጥረት መደረጉም ተገልጿል።

አደጋውን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ 33 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑንና ከአደጋው ጋር በተያያዘ በሠባት ሰዎች ቀላል በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

አደጋውን ለመከለከል የፀጥታና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ላደረገው ድጋፍና ተባባሪነት ፖሊስ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ በደረሰው የእሳት አደጋ የተሰማውን ሃዘን ገልፆ ፥ ወደፊት በምርመራ የደረሰበትን ውጤት ለህዝብ እንሚያሳውቅም በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.