Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እድሳት ሕንጻን መርቀው ከፈቱ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታደሰውን የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንጻ መርቀው ከፍተዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ሕንጻው አህጉራዊ ትልም የታቀደበት ስፍራ ነው ብለዋል።

ከዓመታት በፊት በዚህ አዳራሽ የተደረሰው ስምምነት ለዛሬዋ አፍሪካ መሰረት የጣለ ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡

አዳራሹ ከአዳራሽነት የዘለለ የአፍሪካ ድምጽ መሰሚያ ምልክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ኢትዮጵያ አፍሪካ  በተመድ የጸጥታው ም/ቤት ሪፎርም መደረግ እንዳለበት በጽኑ ታምናለች ብለዋል።

ለአዳራሹ እድሳት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔን አመስግነዋል፡፡

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው÷ ተመድ በሪፎርም ተግባራት ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሁሉም ውክልና ያለበት ድርጅት እንዲሆን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ተመድን ሪፎርም ለማድረግ የተደረሱ ስምምነቶች በፍጥነት መተግበር አለባቸው ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት÷ ይህ ሥፍራ የፓን አፍሪካ አባቶችን የምናከብርበት ነው ብለዋል።

ሊቀመንበሩ የተባበረች አፍሪካን እውን ለማድረግ በሰላምና ደህንነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በህብረቱና በተመድ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ 8 ከፍተኛ መድረኮች መደረጋቸውን ጠቁመው÷ይህም አፍሪካ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ክሌቨር ጋቴቴ÷እድሳቱ የአፍሪካን መልክ ለመቀየር የሚሰራውን ሥራ የሚደግፍ መሆኑን እና አዳራሹ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ መታደሱን ተናግረዋል፡፡

በምስክር ስናፍቅ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.