Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ የህዋ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቨርቹዋል ካምፓስ ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳይ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የህዋ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቨርቹዋል ካምፓስ ለመክፈት ቃል መግባቱ ተገለጸ።

በጣሊያን እየተካሄደ ባለው 75ኛው ዓለም አቀፍ የጠፈር ተመራማሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ከተለያዩ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በዚህም ከአውሮፓ የህዋ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጆሴፍ አሽባቸር፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የህዋ ምርምር ተቋም ሀላፊዎች፣ ከፈረንሳዩ አለም አቀፍ የህዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጆህን ዊንሲቨን (ዶ/ር)፣ ከጣልያን የህዋ ኤጀንሲ ኃላፊዎች እና የጠፈር ተመራማሪዎች ጋር መክረዋል።

በውይይታቸውም ለህዋ ምርምር የሚያገለግሉ የተለዩ እቃዎችን በኢትዮጵያ እንዲመረቱ እና የስራ እድል እንዲፈጥሩ የአውሮፓ የህዋ ኤጀንሲ ለኢትዮጵያ እድሉን እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ፈረንሳይ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የህዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጆህን ዊንሲቨን (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ቨርቹዋል ካምፓስ ለመክፈት ቃል ገብተውላቸዋል።

የአውሮፓ የህዋ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጆሴፍ አሽባቸር በበኩላቸው የህዋ ሳይንስ መሳሪያ ተገጣጣሚ እቃዎች በኢትዮጵያ እንዲመረቱና የስራ እድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ ተናግረዋል።

የስራ እድል መፍጠር፣ በረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠና የወጣቶችን አቅም መገንባት፣ የጋራ የሳተላይት ግንባታ እና መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ውይይቶችን ማድረጋቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.