Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከአጋሮች ጋር እየሰራ ነው-ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የጤና ሚኒስቴር በተፈጥሮ እና ሰውሰራሽ ምክንያቶች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከአጋሮች ጋር እየሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተናገሩ፡፡

ዶ/ር መቅደስ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት የድንገተኛ አደጋ የኤድስ ሪሊፍ እቅድ(ፔፕፋር) ልኡካን ጋር የተወያዩ ሲሆን÷በውይይታቸውም የኤች አይ ቪ ስርጭትን መቆጣጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት÷ሚኒስቴሩ በተፈጥሮ እና ሰውሰራሽ ምክንያቶች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የኤችአይቪ ስርጭትን ለመቆጣጠር ከአጋሮች ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፔፕፋር ፕሮግራም ከሀገሪቱ አሁናዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ እና ከሁኔታዎች መለዋወጥ ጋር የሚስተካከል እንዲሁም ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካባቢዎችን ታሳቢ አድርጎ እንዲሰራም ሚኒስትሯ መክረዋል፡፡

የፔፕፋር ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ጸደይ አለምሰገድ ÷ፔፕፋር የጤና አስተዳደር መረጃ ሥርዓቶችን ጨምሮ የላቦራቶሪ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደርን እና የስትራቴጂካያዊ መረጃ አሰባሰብን ለማጠናከር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ፔፕፋር የጤና ስርአቶችን ለማጠናከርና የአገልግሎት አሰጣጥ ሞዴሎችን ለማሻሻል ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የድንገተኛ አደጋ የኤድስ ሪሊፍ እቅድ (ፔፕፋር) የአሜሪካ መንግስት ከኤች አይ ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን ቫይረሱን ለመለየት፣ መድሃኒት ለማስጀመር እና የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል የአገልግሎት ፓኬጅ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.