የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ጸጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀመረ፡፡
ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው ጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ጉባዔውን ያዘጋጀችበት ዋና ዓላማ ዓለም ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም አህጉራዊ የጋራ ምክክር በማካሄድ የመፍትሔ ሀሳብ ለማመንጨት ጉባዔው መዘጋጀቱ ተመላክቷል።
በጉባዔው አህጉራዊ የጸጥታ ማዕቀፎችን በማጠናከር እና የሀገራትን ወታደራዊ የትብብር አቅም ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ለደኅንነት ስጋቶች ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በጉባኤው የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ተሳታፊዎች አህጉራዊ ወታደራዊ ግብዓቶችንና ትጥቆችን በራስ አቅም ማሟላት በሚያስችሉ ጉዳዮች እና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሚና ላይ በመምከር ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚቀመጡ ይጠበቃል።