Fana: At a Speed of Life!

አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና የዕርስ በዕርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባሉ።

አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱበት ሶስት ክሶች በዛሬ ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

አቶ ታዲዮስ ታንቱ በሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት እና የእርስ በርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በፍትህ ሚኒስቴር በተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዓቃቤ ሕግ በኩል ተደራራቢ አራት ክሶች ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው 1ኛው ክስ ላይ እንዳመላክተው፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/(1)ሀ እና አንቀጽ 257/ሀ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ታዲዮስ ታንቱ በግንቦት 11 ቀን እና በመጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም እና በተለያዩ የዩቲዩብ ቻናሎች ህዝባዊ አመጽ መቀስቀስ ወንጀል የሚል ነው።

በ2ኛ ክስ በተመለከተ ደግሞ የጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃን ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁ 1185/2012 አንቀጽ 4 እና 7/4 በመተላለፍ በታሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ የዩቱዩብ ቻናል ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭተዋል የሚል ክስ በዓቃቤ ሕግ ቀርቦባቸው ነበር።

በ3ኛ ክስ ደግሞ የወንጀል ህግ ከንቀጽ 32/1ሀ እና አንቀጽ 337 በመተላለፍ የመከላከያ ሰራዊትን እቅስቃሴን ለማሰናከልና የመከላከል አደጋ እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ ሀሰተኛ ወሬ በመንዛት ቅስቀሳ ማድረግ ወንጀል የተከሰሱ ሲሆን፤ በ4ኛ ክስ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ቁ 958/2008 አንቀጽ 14 በመተላለፍ ህዝባዊ አመጽ እንዲፈጠር ቀስቃሽ መልክት በድምጽና በተቀሳቃሽ ምስል ተሰራጭቷል የሚል ክስ በዓቃቤ ሕግ በኩል ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በአጠቃላይ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው አራት ክሶች የተጠቀሱትን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸው፤ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዳሉ ያላቸውን ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ምስክርን መርምሮ እንዲከላከሉ በሙሉ ድምጽ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።

አቶ ታዲዮስ እንዲከላከሉ በተሰጠ ብይን መነሻ የተለያዩ የመከላከያ ምስክሮችን በማቅረብ አሰምተው የነበሩ ቢሆንም÷ ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከል አለመቻላቸው ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየትን ለመጠባበቅ ለጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.