የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ኤ350-1000 የተሰኘ አውሮፕላን እንደሚረከብ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተያዘው ጥቅምት ወር ኤ350-1000 የተሰኘውን የመንገደኞች አውሮፕላን እንደሚረከብ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው÷ አየር መንገዱ በአፍሪካ የአቪዬሽን መስክ ያለውን የቀዳሚነት ስፍራ ለማስቀጠል በየጊዜው አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስመጣትና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን በማስፋት ላይ ይገኛል ብለዋል።
አየር መንገዱ በቅርቡ ከኤር ባስ ኩባንያ የሚረከበው ”Ethiopia Land of Origins” በሚል መጠሪያ የተሰየመው ኤ350-1000 አውሮፕላንም በአይነቱ ልዩና በአፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑን አንስተዋል።
አየር መንገዱ ኤ350-900 አውሮፕላኖችን መጠቀም ከጀመረ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን÷ አሁን ላይ 20 የኤ350-900 አውሮፕላኖች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ኤ350-1000 አውሮፕላን ደግሞ 400 መቀመጫዎች ያሉት እና ለደንበኞች የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ያስረዱት።
አየር መንገዱ አሁን ላይ በ147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍ እና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡