Fana: At a Speed of Life!

የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከ4 ወር በኋላ ለስፖርታዊ ውድድር ዝግጁ ይሆናል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በማፋጠን ከአራት ወራት በኋላ ለስፖርታዊ ውድድር ዝግጁ እንደሚሆን የአማራ ክልል ወጣትና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ ገለጹ።

የስታዲየሙ የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ያለበት ደረጃ በክልሉ ሰልጣኝ ከፍተኛና መካከለኛ አመራረ አባላት ዛሬ ተጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ወቅትየክልሉ ወጣትና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ እንዳሉት÷ በ42 ሄክታር መሬት ያረፈው ስታዲየሙ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ በተጨማሪ የራሱን ገቢ እንዲያመነጭ ተደርጎ እየተገነባ ነው።

በሁለተኛው ምዕራፍ የስታዲየሙ ግንባታ የመለማመጃና የመወዳደሪያ ሜዳ፣ የመልበሻ ክፍሎችን፣ ለማታ ጨዋታ የሚያገለግል መብራትና ሌሎች ተግባራትን በማካተት እየተነሳ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከሚያስፈልጉት 52 ሺህ ወንበሮች ውስጥ 45 ሺህ የሚሆኑትን ማስገባት መቻሉን ጠቁመው፤ የ”ቪ.አይ.ፒና የሚዲያ” ቦታዎችም ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን መሰረት በማድረግ እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በሜዳው ላይ የሳር ተከላ ሥራ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደሚካሄድ የጠቆሙት አቶ እርዚቅ የሳር ዘሩና ለሳሩ እድገት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ዝግጁ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የስታዲየሙ ሁለተኛው ምዕራፍ ከአራት ወር በኋላ ለጨዋታ ውድድር ዝግጁ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

የስታዲየሙ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በ1 ነጥብ 8ቢሊየን ብር በጀት እየተካሄደ የሚገኝ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በባህር ዳር ከተማ በመሰልጠን ላይ የሚገኙ የአመራር አባላት ከባህር ዳር ስታዲየም ግንባታ በተጨማሪ አዲሱ የአባይ ድልድይንና ሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.