ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በመጪው ሰኞ ይከበራል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በመጪው ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።
በዓሉ “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ!” በሚል መሪ ሀሳብ በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት የሚከበር ይሆናል፡፡
የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ መከበሩ ለብሔራዊ አንድነት፣ ለሉዓላዊነትና ለኢትዮጵያ ከፍታ ቀጣይነት ብሔራዊ መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል።
ለሀገርና ለሰንደቅ ዓላማ ያለንን እውነተኛ ክብርና ፍቅር ሁላችንም የምንገልፅበትና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ዕለት ይሆናል ሲልም ገልጿል።
በዓሉ በፌደራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች እንዲሁም በየኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ላይ ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ -ሥርዓትን ጨምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገልጿል።