የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ከጥቅምት 5 እስከ 7 በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ከጥቅምት 5 እስከ 7 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) ÷ ጉባዔው “አፍሪካ፤ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
በጉባዔው አህጉራዊ የፀጥታ ማዕቀፎችን ማጠናከርና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ሸብርተኝነትን ለመዋጋትና የጋራ የደህንነት ስጋቶችን ለመፍታት አጋርነትን ስለማጠናከር እና በመከላከያ ኢንዱስትሪ መስክ አብነት የሆኑ ሀገራት ተሞክሮዎች የሚጋሩበት ነው ብለዋል።
ጉባዔው አፍሪካ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ በሰላም ማስከበር ያላትን ሚና ስለማሳደግ እና በሰብዓዊ ዕርዳታና በአደጋ ወቅት ያለውን የትብብር አቅም በማሳደግ ላይ ያተኩራል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡