ኢትዮጵያና ኬንያ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ኬንያ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግና ትብብራቸውን አጠናክረው መቀጠል በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ ልዑክ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ጋር የልምድ ልውውጥም አድርጓል፡፡
በመድረኩ የኬንያ የዳያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሮስሊን ንጆጉን ጨምሮ በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደርና የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው÷ ኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ስራዎችን ለማጎልበት ያለፈችባቸው ህጋዊ፣ ተቋማዊና መዋቅራዊ ሂደቶችን እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ለዳያስፖራው ባቀረበቻቸው ተከታታይ ሀገራዊ ጥሪዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ለልዑካን ቡድኑ ማብራራታቸውን የዳያስፖራ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት÷ ስለተደረገላቸው አቀባበልና ገለፃ አመስግነው ኢትዮጵያ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ተቋምና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር መስራት መቻሏ እንደ ተሞክሮ የሚወሰድ ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኬንያ በርካታ ዳያስፖራ ያላቸው ጎረቤት ሀገራት መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡