ኢትዮጵያ ለጋራ የውሃ ተጠቃሚነት አሁንም የፀና መርህ እንዳላት ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለጋራ የውሃ ተጠቃሚነት ያላት መርህ አሁንም የፀና መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የውሃ ዲፕሎማሲና የኮሙኒኬሽን ፎረም ላይ ሐብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአሁኑ ዘመን ውሃ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ አግባብ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶቿን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለመጠቀም ያላት አቋም የፀና መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያን ዕውነት በማሳወቅ ሂደት ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ከውሃ ዲፕሎማሲና እና ፖለቲካ ጋር በተገናኘ መነሻ ፅሁፍ ቀርቦም ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።
የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ያቀፈው የውሃ ዲፕሎማሲና የኮሙኒኬሽን ፎረሙ ከሁለት ዓመት በፊት በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተጀመረ ነው።
በመድረኩ የዘርፉ ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በወንድሙ አዱኛ እና ሙክታር ጠሃ