የዐደባባይ በዓላት ለከተማችን ተጨማሪ ውበት ናቸው- ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዐደባባይ በዓላት ለከተማችን ተጨማሪ ውበት እና የቱሪስት መስኅብ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በአዲስ አበባ የዐደባባይ በዓላት በድምቀት ተከብረው እንዲጠናቀቁ አስተዋጽዖ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡
ከአዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ በመዲናዋ የተከበሩ በዓላት ሰላማዊ፣ የተረጋጋ፣ ደማቅ፣ ሕዝቡን ባከበረ መንገድ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የጸጥታ አካላት፣ በየደረጃው የሚገኙ የከተማ አሥተዳደሩን አመራሮች እንዲሁም መላው የከተማውን ሕብረተሰብ አመስግነዋል::
የዐደባባይ በዓላት ለከተማችን ተጨማሪ ውበት እና የቱሪስት መስኅብ ናቸው ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ነዋሪውን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ ከተማችን አዲስ አበባን ሰላማዊ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የጀመርነውን ሥራም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው÷ የዐደባባይ በዓላቱ በድምቀት ተከብረው ለመጠናቀቃቸው የከተማ አሥተዳደሩ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ለሠራው ሥራና ለተገኘው ውጤት አመስግነዋ፡፡
ተቀናጅቶ መሥራቱ በቀጣይም በይበልጥ ውጤታማ ስለሚያደርገን በጋራ መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል::