ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ዳይሬክተር ጄነራል ኤሚ ፖፕ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በቅንጅት መስራት በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በዚህም ሁለቱ ወገኖች የህገ ወጥ ፍልሰት ተግዳሮቶችን በዘላቂነት መፍታት እና የውጪ ሀገር ስራ ስምሪት ለዘላቂ ልማት የሚያበረክተዉን አስተዋፅዖ ማሳደግ በሚቻልባቸው የትብብር ሀሳቦች ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ተመስገን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ፍልሰተኞች መጠለያ መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተሩ፤ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ህገወጥ ፍልሰትን ከመከላከል፣ ከፍልሰት ተመላሾች እና ተፈናቃዮችን ከመደገፍ አኳያም ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡