Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ለሁለንተናዊ የእድገት ትግበራ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍን በማላቅ ለሁለንተናዊ የእድገት ትግበራ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)፣ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ወጣቶች በተገኙበት 3ኛው የፓን አፍሪካ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮንፈረንስ መካሄድ ጀምሯል።

ዘግይታ ወደ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የገባችው አፍሪካ ዘርፉን ለችግሮች መፍቻና ለፈጣን እድገት በሰፊው ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባት ተመላክቷል።

በኮንፈረንሱ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በተለያዩ ዘርፎች ያለውን አስተዋጽዖ እና አተገባበር የሚያስረዱ ጥናታዊ ጽሁፎችና ምርምሮች ቀርበዋል።

በዚሁ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ÷ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የላቀ ስራ ለመተግበር ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ ስራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡

የዘርፉን ባለሙያዎች በትምህርት፣ በስልጠናዎችና ምርምር በማብቃት አፍሪካውያን ይህን ምህዳር ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት መካሔድ በጀመረው 3ኛው ዙር ፓን አፍሪኮን ኤ.አይ 2024 “አፍሪካን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማላቅ” በሚል መሪ ቃል ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም መሰል መድረኮችን ስናዘጋጅ አፍሪካ ቴክኖሎጂን የምትቀበል ሳይሆን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አብዮትን ለመምራት ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።

በፍሬህይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.