Fana: At a Speed of Life!

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረቡለትን ዕቅዶች መርምሮ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ምክር ቤቱ 6ኛ የፓርላማ ዘመን 4ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን በምክር ቤቱ የጉባዔ አዳራሽ ለዕለቱ የተያዙ አጀንዳዎችን በማጽደቅ ነው ውይይቱን ማካሄድ የጀመረው፡፡

በዚሁ ወቅትም 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 3ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ቃለጉባዔውን መርምሮ በማጽደቅ ምክር ቤቱ ጉባዔውን ማካሄድ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፣ የመንግሥታት ግንኙነት የዲሞክራሲ አንድነትና የሕገ-መንግሥት አስተምኅሮ ቋሚ ኮሚቴ፣ የማንነት፣ የአሥተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ፣ የሕገ-መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምኅሮ ማዕከልና የሕገ-መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በመወያየት አጽድቋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም የቀረቡላቸውን ዕቅዶች መሠረት በማድግ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን÷ የየቋሚ ኮሚቴዎቹ አመራሮች ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የቀረቡ ዕቅዶች እንዲጸድቁ ለድምጽ አቅርበው ጉባዔው በሙሉ ድምጽ ደግፎ አጽድቋቸዋል መባሉን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.