Fana: At a Speed of Life!

ሕዝቡን እየፈተኑ የሚገኙትን የኑሮ ውድነትና ሌብነት ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነሰ ይሰራል -ፕሬዚዳንት ታዬ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2017 በጀት ዓመት ሕዝቡን እየፈተኑ የሚገኙትን የኑሮ ውድነት፣ ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነሰ በትኩረትና በትብብር እንደሚሰራ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በወቅቱ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና አመርቂ እድገት አስመዝግባለች፡፡

እድገቱን በተያዘው በጀት ዓመት ለማስቀጠል ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተኑ የሚገኙትን ተግዳሮቶች ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቀነስ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በተለይም የኑሮ ውድነትን፣ ሌብነትን እና ብልሹ አሰራርን እንዲሁም የጸጥታ ስጋት፣ ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድን ለመቀነሰ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሒደት ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የጸዳች እንድትሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረትና በትብብር እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡

የፍትሕ ስርዓቱን ጤናማነት እና የሰብዓዊ መብት አያየዝን ለማሻሻል በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም ለምክር ቤቶቹ አስረድተዋል፡፡

በኢትጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ የፍትህ መዛባቶች እና የመብት ጥሰቶችን በአግባቡ ለመቋጨት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.