በአዲስ አበባ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ላዳ ታክሲዎች በአዳዲስ ታክሲዎች ሊተኩ ነው
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 5 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በመዲናዋ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ላዳ ታክሲዎች በአዳዲስ ታክሲዎች እንደሚተኩ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ የታክሲና የሀይገር ባስ ማህበራት ለተገልጋዩ ክብርን በመስጠት ለማገልገል የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ ማድረጊያ መድረክ ተከናወኗል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት ኢንጂነር ታከለ ኡማ አነስተኛ ታክሲዎችና ሀይገር ባሶች ለነዋሪው እየሰጡ ላለው አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።
የታክሲ ባለንብረቶች በተለያዩ ጊዜያት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አስተዳደሩ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በእድሜ ያረጁ አነስተኛ ታክሲዎች አዳዲስና የመጫን እቅማቸው ከፍ ባሉ አነስተኛ ታክሲዎች እንዲተኩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለዚህም ባለንብረቶችን ከባንክ ጋር የማስተሳሰር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የታክሲና የሀይገር ባስ ባለንብረቶች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ 13 የታክሲ እና ሶስት የሀይገር ባስ ማህበራት ተሳትፈዋል።
መርሐ ግብሩ በተለይ አረጋውያን፣ ለነፍሰጡሮች እና አካል ጉዳተኞችን በተሻለ መንገድ ለማገልገል የሚያግዝ ነው ተብሏል።
መርሃ ግብሩ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በተደራጀ መንገድ በነጻ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑም በዚህ ወቅት ተገልጿል።
የተለያዩ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ባለንብረቶች ለኩላሊት ታካሚዎች፣ ለነፍሰ ጡሮች እንዲሁም ለመምህራን በነጻ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ይታወቃል።
በአልአዛር ታደለ