Fana: At a Speed of Life!

መዲናዋን የቱሪስት መዳረሻ ካደረጓት በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ከተማን የቱሪስት መዳረሻ ካደረጓት የአደባባይ በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡

ከንቲባዋ የኢሬቻን በዓል አስመልከተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ የኢሬቻ በዓል የክረምቱ ጭጋግ አልፎ ወደ ጸደይ ሲሸጋገር ተለያይቶ የቆየው ሁሉ የሚገናኝበት የአንድነት እና የወንድማማችነት መገለጫ በዓል ነዉ ብለዋል።

ኢሬቻ የገዳ ስርዓት አንዱ ምሰሶ መሆኑን ጠቅሰው÷ የምስጋና፣ የአንድነት፣ የሰላም፣ የእርቅ እና የይቅርታ ተምሳሌት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት በዓል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በብዝሃነት አጊጣ፣ በበጎነት ተኩላ፣ በትጉህ እጆች ያበበችው የሁላችን ጎጆ አዲስ አበባ እንግዶቿን በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተቀብላ እያስተናገደች የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስቶችን የምትስብ የጋራ መድመቂያ ከተማችን ሆናለች ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል፣ የቱሪስት መዳረሻ ካደረጓት የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉ ለህዝብ ትስስር፣ አብሮነት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የላቀ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ይህን በመረዳት የከተማው ነዋሪ እስካሁን እንግዶችን በመቀበል እና በማስተናገድ ላሳየው አብሮነት እና ወንድማማችነት ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.