Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሪክስ የሚኒስትሮች ቅንጅት ኮሚቴ 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ የብሪክስ የሚኒስትሮች ቅንጅት ኮሚቴ ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

በስብሰባው የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ ስትራቴጂ፣ የከፍተኛ ባለሞያዎች ኮሚቴ ያካሄደውን የኢትዮጵያ የዓመቱ የብሪክስ ተሳትፎ ግምገማ፣ ኢትዮጵያ ስለተሳተፈችባቸው ሁለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባዎች ሪፖርቶች ውይይት መደረጉ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የብሪክስ ሴክሬታሪያት ሪፖርቶች እና በጥቅምት ወር በሩሲያ ስለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ዝግጅትን በተመለከተ ሰፊ ውይይት መካሄዱ ተጠቁሟል፡፡

የብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ÷ የብሪክስ ማዕቀፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ተጨማሪ ከፍተኛ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከሆነች ጀምሮ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ የማዕቀፉ መድረኮች ላይ በንቃት መሳተፏን አብራርተዋል።

በብሪክስ የኢትዮጵያ ም/አስተባባሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ዲፕሎማሲያችንን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።

የቅንጅት ኮሚቴው አባላት በቀጣይ ኢትዮጵያ በብሪክስ ማዕቀፍ ጉልህ ሚና እንድትጫወት በትብብር በንቃት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጸው፤ በቀጣይ መድረኩን በመጠቀም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በንቃት ተሳትፎ እንደሚደረግ አንስተዋለ።

የሚኒስትሮች ቅንጅት ኮሚቴ የኢትዮጵያ የብሪክስ ተሳትፎ ስትራቴጂ የመጨርሻ ቅርጽ ላይ መስማማቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ የዓመቱ የብሪክስ ተሳትፎ ከገመገመ በኋላ ቀጣይ ተሳፎን ለማጠናከር እና የኢትዮጵያ ሚና እና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ሀሳቦች መለየታቸውም ተጠቁሟል፡፡

መድረኩ በተለይም በጥቅምት ወር የሩሲያ ከተማ በሆነችው ካዛን ለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ዝግጅት ከየኮሚቴው አባልት የሚጠበቁ ሥራዎችን በመለየት ተጠናቅቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.