ህብረተሰቡ ለክልሉ ልማትና እድገት ተባብሮ ሊሰራ ይገባል-ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የተገኘውን ሰላም በማጠናከር ህብረተሰቡ ለክልሉ ልማትና እድገት ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድና ምክትላቸው ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በኢታንግ ከተማ ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።
ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት÷ ህዝቡ አሁን ላይ የተገኘውን ሰላም በማጽናት ለክልሉ ዘላቂ ልማትና እድገት በትብብር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የተፈለገውን ልማት ለማምጣት ሁሉም የሰላም አምባሳደር በመሆን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ መንግስት ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድሯ ማረጋገጣቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።