Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 5 ሺህ 300 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣መስከረም 22፣ 2017(ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ 5 ሺህ 300 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄሎ ኡመር (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አስመዝግበው በመንግሥት ሙሉ ወጪ የሚማሩ 4 ሺህ 402 ተማሪዎች ለውድድር ተመዝግበው 2 ሺህ 660 ፈተናውን እንዳለፉም ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲ የመግቢያ ነጥብ በማምጣትና በራሳቸው ከፍለው ለመማር ካመለከቱት 7 ሺህ 537 ተማሪዎች መካከል ደግሞ 2 ሺህ 640 ተማሪዎች የመግቢያ ፈተናውን አልፈዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ዩኒቨርሲቲው 5 ሺህ 300 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን ገልጸው÷ ከእነዚህ መካከል ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ 200 ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።

በአዲሱ የተማሪዎች ቅበላ መስፈርት መሰረት ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሠራሮች እየተተገበሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.