አቶ ጥላሁን ከበደ ከመከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖችን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በሀገራዊና ክልላዊ የጸጥታ ሁኔታዎች ላይ በትኩረት መምከራቸውን የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
መድረኩ አሁናዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የጸጥታ መዋቅሩ በቅንጅት የሚሰራቸው ተግባራት ተጠናክረው በሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቅሷል።
አቶ ጥላሁን÷የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል ።
ከክልሉ የውስጥ የሰላም በተጨማሪ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ ከክልሎች ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች በበኩላቸው÷የክልሉ መንግስት ሰላምን ለማስጠበቅ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግበራት አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
መከላከያ ሠራዊት በቀጣይ የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።