በአፋር ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር መድረክ አስጀምሯል፡፡
በመድረኩ ላይም ከ49 ወረዳዎች የተወጣጡ 802 የሕብረተሰብ ተወካዮች እና 771 ባለድርሻ አካላት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው፡፡
ከየወረዳው ከተወጣጡ ተሳታፊዎች በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማኅበራት እንዲሁም የመንግሥት አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ መድረኩ የሕብረተሰብ ተወካዮች ለሀገራዊ መግባባት ይበጃሉ ያሏቸውን ሀገራዊ ጉዳዮችን በአጀንዳነት አንስተው በሕዝባዊ ውይይት የሚዳብርበት ነው ።
ለስድስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ ተሳታፊዎች ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳውን በመረዳት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
በምንተስኖት ሙሉጌታ