Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ሂደት፣ በሕግ ትብብር ጉዳዮች እና በጋራ ጥቅም ላይ አብረው ለመሥራት ተስማሙ፡፡

በፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታ ተስፋዬ ዳባ የተመራ ልዑክ በአዘርባጃን እየተካሄደ በሚገኘው 29ኛው ዓለም አቀፍ የዐቃቤ ሕጎች ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

ከጉባዔው ጎን ለጎን አቶ ተስፋዬ ከአዘርባጃን ፍትሕ ሚኒስትር ፋሪድ አምዶቭ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር በትብብር በመሥራት የተለያዩ ልምዶችን መቅሰም እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡

የሕግና ፍትሕ ሥርዓትን ለማሻሻል እና የአንድ ማዕከል የሕዝብ አገልግሎት ልምድ ለመተግበር አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ተግባራት (የጋራ የሥራ ቡድን የማደራጀት፣ የሁለትዮሽ ስምምነት ረቂቅ ሠነዶች እና መሰል ሥራዎች) በጋራ ለመሥራት እንደሚፈልጉም አስረድተዋል፡፡

ከአዘርባጃን ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት እንዲኖር እና በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የልምድ ልውውጥ እንዲኖር እንፈልጋለን ማታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የአዘርባጃን ፍትሕ ሚኒስትር በበኩላቸው÷ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርመው እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ትብብሮች ማዕቀፍ ስር ሆነው በጋራ ጥቅም ተመስርተው እንደሚሠሩ አብራርተዋል፡፡

በተቋማቸው የተሠሩ የፍትሕ ሥርዓት ዲጂታላይዜሽን ፣ ትምህርትና ሥልጠና፣ ሌሎች የተቋሙን ሥራዎች እና በሀገራቸው ያለውን የፍትሕ ሂደት በተመለከተም አብራርተዋል፡፡

ሁለቱም የሥራ ኃላፊዎች በፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ሂደት እና በሕግ ትብብር ጉዳዮች እና በጋራ ጥቅም ላይ አብረው ለመሥራት መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.