Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ የኤምባሲ ሰራተኞቿ ከሌባኖስ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ሌባኖሰ የሚገኙ የኤምባሲ ሰራተኞች ቤተሰቦቻቸውን ይዘው  እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷ ተገለፀ፡፡

ትዕዛዙ የሌባኖሱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቡድን ሂዝቦላህ መሪ ሲያድ ሀሰን ናስራላህ በእስራኤል የአየር ሀይል መገደሉን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት በመፈጠሩ ነው ተብሏል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ÷በቤይሩት የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች ያለ ቅደመ ፈቃድ በግል መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ገደብ መጣሉን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በሚሲዮኑ ውስጥ በደህንነት ሃላፊነት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች መጠነኛ የእንቅስቃሴ ገደብ ሊጣልባቸው እንደሚችል አመላክቷል፡፡

እስራኤል ትናንት ምሽት በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሂዝቦላህን ለ30 ዓመት የመሩት ሀሰን ናስራላህን እና ሌሎች የቡድኑን አመራሮች መግደሏን ያስታወቀች ሲሆን ሂዝቦላህም የቡድኑ ቁልፍ ሰው መሞቱን አረጋግጧል፡፡

ጥቃቱን ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩ የተገለፀ ሲሆን÷ በቀጣናው ኢራን በእስራኤል ላይ የአፀፋ ጥቃት እንደምትፈፅም ተሰግቷል፡፡

በእስራኤል እና ሂዝቦላህ መካከል የሚደረገው ጦርነት የቀጠለ ሲሆን÷በዛሬው እለት ከሂዝቦላህ በተጨማሪ የየመኑ ሀውቲ ቡድን ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን መተኮሱ ተሰምቷል፡፡

እስራኤል ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በሌባኖስ ላይ ባካሄደችው ዘመቻ ከ800 በላይ ሰዎች ሞተዋል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.