Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የለሚ ብሔራዊ የሲሚንቶ ፋብሪካን መርቀው ሥራ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀን 150ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም ያለውን የለሚ ብሔራዊ የሲሚንቶ ፋብሪካ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ይህን ተከትሎ ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷” ይህ ሜጋ ፕሮጀክት የመንግሥታችን በፍጥነት፣ በግዝፈት እና በንፅህና የመገንባት ጽኑ አቋም ማሳያ ነው” ብለዋል።

እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በፍጥነት እና በብቃት አጠናቅቆ ዝግጁ የማድረግ ተምሳሌት መሆኑንም ገልፀዋል።

ይህ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ተደምረው የሚያመርቱትን 50 ከመቶ የሚያመርት ፋብሪካ እውን እንዲሆን ለተሳተፉ በሙሉም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከሁለት አመታት በኋላ ወደዚህ ስፍራ ስመለስ የአመራር መርሆዎቻችን ማሳያ በሆነው በሥራው ፍጥነት ተደንቄያለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ በመሰል ጠንካራ ሥራ መጪው ትውልድ ድህነትን እንደማይወርስ ይልቁንም ለእድገት እና ብልጽግና ጥሩ መደላድል እንደሚጠብቀው ያሳያል ብለዋል።

እንደ ለሚ ያሉትን የኢንደስትሪ ፕሮጀክቶች በመላው ሀገሪቱ ካባዛን በሥራ ፈጠራ እና በሀገራዊ እድገት ላይ የሚኖረው የመባዛት ፍሬ አቻ የማይገኝለት ይሆናል ሲሉም ነው የገለፁት።

በተለይም በብረት ምርት፣ በማዳበሪያ ምርት ብሎም በሰፊው የኢንደስትሪ እና ግብርና ልማት አብዮት የሚኖረው ተፅዕኖ ሰፊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልቅ ሀገራትን የሚገዳደሩ ፈተናዎች ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው መፍትሔዎችን ይሻሉ ያሉት ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር)÷ በመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የሚኖር የጋራ ትብብር እምቅ ሀብትና እድሎችን ለመጠቀም ብሎም ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ መሆኑን አመልክተዋል።

በመሰል ሥራዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ማሻሻል እንዲሁም ክብር ያለው አኗኗር እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የጠቆሙት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.