Fana: At a Speed of Life!

መስቀል የትዕግሥት፣ የዕርቅና የሰላም ምልክት መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መስቀል የትዕግሥት፣ የዕርቅና የሰላም ምልክት መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የመስቀል በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ቅዱስ መስቀል ከኃጢአት ጥላ፣ ከጥፋት ጨለማ የወጣንበት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት የነፍሳችን ብርሃን፣ የሕይወታችን መብራት ነው ብለዋል።

ከበረቱ፣ ከታገሉ እና ከጸኑ የማይሳካ ነገር እንደሌለ፤ የጸና የድል ባለቤት እንደሚሆን ከመስቀል ደመራ እንማራለን ሲሉ ገልጸዋ፡፡

ተስፋ ሳይቆርጥ ለሚተጉ እንደ ንግሥት እሌኒ ሕልሙ እውን ሆኖ ማየቱ አይቀርም በማለት ጠቅሰው፤ ደመራ ከተለያዩ አካባቢዎች በተሠበሠቡ ችቦዎች ተደምሮ ብርሃን መስጠቱ አንድነትን፣ ኅብረትን፣ ፍቅርን እና መረዳዳትን የሚያስተምር መሆኑን ተናግረዋል።

በሚገጥሙን ፈተናዎች ሁሉ ሳንንበረከክ እንደደመራዉ በአንድነት ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

የድካማችንን ዉጤት ማየት እንደምንጀምር በማመን በፍቅር አንድ ሆነንና ተሰባስበን ከሰራን ጠንካራ፣ የበለፀገች፣ ዘላቂ ሰላሟ እና አንድነቷ የፀና ህብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን ማየታችን አይቀርም ብለዋል።

ለመስቀሉ ክብር ስንሰጥና፣ የደመራውን በዓል ስናከብር መስቀል የትዕግሥት፣ የዕርቅና የሰላም ምልክት መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል። በመስቀሉ የተደረገው ዕርቅና፣ የተገኘው ሰላም በሁላችን ልብ መገኘት ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል።

ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ያገኘችው በእምነት ፅናት፣ በብዙ ፍለጋ፣ ትዕግሥትና፣ ድካም ነው ያሉት አቶ አረጋ፤ እኛም ለትጋታችን መልስ፣ ለፍለጋችን ምልክት እስከምናገኝ በጽናት መስራት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ስለሆነም አንድነታችን ፍፁም በሆነ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ላይ በመገንባት እንደ ደመራችን ብርሃን ተስፋችንን እናድምቅ፤ በአንድነት ተሰባስበን የሚገጥሙንን ፈተናዎች በጽናት እንሻገር ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.