Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልእክታቸው÷ በዓሉን ስናከብር በመስቀሉ የተገለጠውን የክርስቶስ ቤዛነት፣ ፍቅር እና እውነትነት ዓርዓያ በመከተል እርስ በርሳችን በመዋደድ ልዩነትን፣ መራራቅን እና አለመግባባትን በማስወገድ ህብረ ብሄራዊ አንድነነትን ለማጠናከር ቃል በመግባት ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

አንዳችን ከአንዳችን በፍቅርና በመተሳሰብ መኖርም ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የመስቀል በዓል የፍቅር፣ የመረዳዳት እና የይቅርታ በዓል በመሆኑ ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን ከመርዳት ባሻገር በደልን ይቅር ለእግዚአብሔር በመባባል ሊሆን እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የመስቀል በዓል በክልሉ ህብረተሰብ ዘንድ የተስፋ፣ የልምላሜ እንዲሁም በአዲስ መንፈስ ለአዲስ ስኬት ጉዞ የሚጀመርበት የመጀመሪያ ዕለት ተደርጎ ይቆጠራል በማለት ጠቅሰው፤ ሁሉም በተሰማራበት ውጤት በማስመዝገብ የክልሉን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ መትጋት አለበትም ነው ያሉት፡፡

የመስቀል በዓል በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተ የሚገኝ የሀገር ሀብት በመሆኑ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለትውልድ እንዲተላለፍ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናበረክት ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በክልሉ በወርሃ መስከረም የሚከበሩ የተለያዩ የአደባባይ በዓላት መኖራቸውን ጠቅሰው÷ ባህላዊ እሴትን ጠብቀው እንዲቀጥሉ በማድረግ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.