Fana: At a Speed of Life!

የመስቀል ደመራ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ ተገለፀ።

በዚህም ነገ ከረፋዱ 5 ሰአት ጀምሮ እስከ መርሀ ግብሩ ፍፃሜ ድረስ ለተሽከርካሪዎች ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል። በዚህም መሠረት ፦

• ከቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ላይ፣
• ከቦሌ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኦሎምፒያ አደባባይ ላይ፣
• ከመስቀል ፍላወር ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ ጋዜቦ አደባባይ ላይ፣
• ከአጎና ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ለከባድ ተሽከርካሪ አጎና ሲኒማ አጠገብ እንዲሁም ለቀላል ተሽከርካሪ ጥላሁን አደባባይ (አራተኛ ክፍለ ጦር ላይ)፣
• ከለገሀር መብራት ወደ መስቀል አደባባይ ለገሀር መብራት ላይ፣
• ከቴሌ ማቋረጫ ወደ ስታዲየም ለሚጓዙ ቴሌ ማቋረጫ፣
• ከራስ ሆቴል ወደ ስታድየም ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ራስ ሆቴል ላይ፣
• ከሃራምቤ መብራት ወይም ከአምባሳደር ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ሃራምቤ መብራት ላይ፣
• ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አጠገብ፣
• ከዛንቺስ ሼል ወደ ባምቢስ የሚወስደው መንገድ ከዛንቺስ ሼል አጠገብ እንዲሁም
• ከጁፒተር ሆቴል ወደ ECA የሚወሰደው መንገድ ባምቢስ ሳልኮት ህንፃ አጠገብ ከተጠቀሰው ሰአት ጀምሮ ለተሽከርካሪ ዝግ መሆኑንና በተገለፁት መስመሮች ላይ ተሽከርካሪዎችን ለአጭርም ይሁን ለረዥም ጊዜ ማቆም የተከለከለ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በዚህም አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀምና የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚያሳይዋቸው መንገድ በመጓዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።
በዓሉ ያለ ፀጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን ያስታወሰው ፖሊስ፤ ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-11-01-11 እንዲሁም በ991 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥም መልዕክት ተላልፏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.