Fana: At a Speed of Life!

ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን በመቅረፅ ሒደት ውስጥ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ምንድናቸው?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር አጀንዳዎችን በማሰባሰብ እና በመቅረፅ ሂደት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

ኮሚሽኑ በዋነኛነት ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ግልፅ፣ አካታችና አሳታፊ በሆነ መንገድ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በየፈርጁ ለይቶ ካቀረበ በኃላ ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሆኑ አጀንዳዎችን ይቀርጻል፡፡

በአጀንዳ ቀረፃ ሒደት ውስጥ ኮሚሽኑ ከግምት የሚያስገባቸው መርሆች ያሉት ሲሆን÷ እነዚህም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1. ለምክክር ጉባዔው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን መመጠን

ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ እያለፈች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑም በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ሲቋቋም በተለያዩ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነት እና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ እነዚህን ልዩነቶች በምክክር እንዲጠቡ ለማድረግ ነው፡፡

በአንዳንድ መድረኮች እንደሚስተዋለው ኮሚሽኑ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ችግሮች መፍታት የሚችል ተደርጎ በመታሰቡ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ የሚነሱ ጉዳዮችን እንደሚያስተናግድ የመጠበቅ አዝማሚያ ይታያል፡፡ ሆኖም ኮሚሽኑ የተቋቋመው ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚረዱ ብሎም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲመነጩ ሁነኛ ሚና ለመጫወት እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን (አጀንዳዎችን) በመቅረጽ ወደ ምክክር ጉባኤው እንዲቀርቡ ያደርጋል፡፡

2. ድምፃቸው ጎልቶ የማይሰማ (minorities) የማህበረሰብ ክፍሎች አጀንዳዎች በአግባቡ መካተታቸውን ማረጋገጥ

በተለያዩ ሀገራት በሚተገበሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስርዓቶች ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ የማይሰማ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ኮሚሽኑ የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች መሰረት አድርጎ ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡትን ሲቀርፅ የእነዚህን ማህበረሰብ ክፍሎች ድምፅ ማንፀባረቅ መቻሉን የማረጋገጥ ሀላፊነት አለበት፡፡

3. ወቅታዊና እጅግ አንገብጋቢ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት

ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የሚሰበስባቸው ቀጥሎም የሚቀርፃቸው አጀንዳዎች በቁጥር ብዙ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢገመትም ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ምክክር ሊደረግባቸው የሚገቡ እና አፋጣኝ መፍትሔን የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔው እንዲሚያቀርቡ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.