Fana: At a Speed of Life!

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳይጀመሩ የቆዩ ፕሮጀክቶች ሥራ ዘንድሮ ይጀመራል – ተቋሙ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሦስት ዓመት በፊት ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ኃይል ለማቅረብ በዕቅድ ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘው በጀት ዓመት ለማስጀመር እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ የአፈፃፀም ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ ዳይሬክተር አክሊሉ ታረቀኝ እንደገለፁት÷ ለደብረ ማርቆስ-ቡሬ፣ ገንዳ አርባ፣ ወይናታ እና ጎንደር-ዳንሻ- ሁመራ- ባዕከር የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ኃይል የሚያቀርቡ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ባለመገኘቱ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ሳይጀመሩ ቆይተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ተቋሙ በዕቅድ የያዛቸውን ሥራዎች እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበት መቆየቱን አስታውሰው÷ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቶችን ግንባታ ማስጀመር የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም የደብረ ማርቆስ – ቡሬ፣ ገንዳ አርባ እና ወይናታ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

አሁን በተገኘው የውጭ ምንዛሪ ሦስቱ ፕሮጀክቶች በተያዘው የበጀት ዓመት እንደሚጀመሩ ማረጋገጣቸውን የተቋሙ መረጃ አመላክቷል፡፡

የፕሮጀክቶቹን ግንባታ ለመጀመር ሲታቀድ ለአራቱም ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ 83 ቢሊየን ብር የግንባታ ወጪ ተመድቦላቸው እንደነበርም ነው ያስታወሱት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.