Fana: At a Speed of Life!

በሂዝቦላህ ላይ የተፈጸመው የኤሌክትሮኒክስ ጥቃት በቀጣናው አዲስ ውጥረት መፍጠሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሌባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሂዝቦላህ ላይ ያነጣጠረው የመገናኛ ሬዲዮ እና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪዎች ጥቃት በመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና አዲስ ውጥረት መቀስቀሱ ተገልጿል፡፡

በሌባኖስ ፔጀርና ዎኪ ቶኪ የተሰኙ ሂዝቦላህ በብዛት የሚጠቀማቸው መገናኛ መሳሪያዎች መፈንዳታቸውን ተከትሎ ከ20 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ከሞቱት ውስጥ ከ8 በላይ የሚሆኑት የሂዝቦላህ አባላት ሲሆኑ÷በሌባኖስ የኢራን አምባሳደር ሞይታባ አሚኒ በፍንዳታው አንድ አይናቸውን ማጣታቸው ተሰምቷል፡፡

በደህንነት ካሜራዎች የተቀረፁ ምስሎች በሌባኖስ፣ ሶሪያና ቤሩት በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ሰዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩት የፔጀርና ወኪ ቶኪ መሳሪያዎች በድንገት ሲፈነዱ ያሳያሉ፡፡

ጥቃቱን  ፈጽማለች በሚል የተወነጀለችው እስራኤል እስካሁን ስለ ጉዳዩ ያለችው ነገር  አለመኖሩ የተመላከተ ሲሆን÷ ለአሜሪካ ግን በጥቃቱ ዙሪያ ገለጻ ማድረጓ ተጠቁሟል፡፡

በአንጻሩ የሌባኖስ የደህንነት ምንጮችየእስራኤሉ የስለላ ተቋም ሞሳድ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቹ ላይ በቀላሉ የማይመረመር እና ኮድ የሚቀበል ፈንጅ ቀብሮ ነበር ሲሉ ወንጅለዋል፡፡

የምርቶቹ ባለቤት የሆነው የታይዋኑ ጎልድ አፖሎ ኩባንያ በበኩሉ ከፍንዳታው በስተጀርባ እጁ እንደሌለበት ገልጾ÷የፔጀርና ዎኪ ቶኪ ምርቶች መቀመጫውን ቡዳፔስት ባደረገው የቢኤሲ ኩባንያ የተመረቱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ ኩባንያው ይህን ያለው የሂዝቦላህን ቁጣ ለማብረድና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶቹ ከገብያ እንዳይወጡ በመስጋት ነው መባሉን አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.