በኮምቦልቻ በቀን 30 ሺህ ሊትር የሚያመርት የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮምቦልቻ ከተማ በቀን 30 ሺህ ሊትር ማምረት የሚችል የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ ጀምሯል።
ፋብሪካውን በአደፋ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ግሩፕ አባይ ወተት ነው በ46 ሚሊየን ብር ካፒታል ያስገነባው፡፡
የፋብሪካው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አባይ ድግስ እንዳሉት÷ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካው በኮምቦልቻና አጎራባች ዞኖች ላሉ 5 ሺህ ያህል ወተት አምራቾች የገበያ እድል ይፈጥራል፡፡
ለአርሶ አደሮቹ የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር ለዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩንም አመላክተዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ወንደሰን ልሳነ ወርቅ በበኩላቸው÷በርካታ እንስሳት አርቢዎች ባሉባት ከተማ የፋብሪካው ሥራ መጀመር ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
በዘርፉ ተሰማርተው ወደ ሥራ ያልገቡ ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በእሌኒ ተሰማ