Fana: At a Speed of Life!

የበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የአስክሬን ሽኝት በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የአስክሬን ሽኝት በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በሽኝት ስነ-ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተገኝተዋል።

የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የኢሶሕዴፓ አመራር እንዲሁም ከቅርብ ወዳጃቸውና ቤተሰባቸው የስንብት መልዕክት በሽኝት መርሐ-ግብሩ እደሚቀርብም ነው የተጠቆመው፡፡

የሽኝት መርሐ-ግብሩ ሲጠናቀቅም የቀብር ስርዓቱ በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ዛሬ 8 ሰዓት ላይ ይፈጸማል።

በየነ (ፕ/ር) በገጠማቸው የልብ ህመም በሀገር ውስጥ እና በኬኒያ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ማክሰኞ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2012 ዓ.ም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

በኢንስቲትዩቱ ለተመራማሪዎች የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና በማመቻቸት ሙያቸውን እንዲያሳድጉ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሲሆን፥ ጀማሪ ተመራማሪዎችም አቅማቸውን አጎልብተው ትርጉም ያለው የምርምር ስራ እንዲሰሩ ጥረት ማድረጋቸው ይነገራል፡፡

ሁሉም የምርምር ስራዎች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ የምርምር ውጤቶች ለህብረተሰቡ እንዲደርሱና የሚመለከተው አካልም እንዲጠቀምባቸው በማድረግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በፍሬሕይዎት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.