የብሪታኒያን አግሪ ቢዝነስ ትሬድ ሚሽን በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታኒያ አግሪ ቢዝነስ ትሬድ ሚሽን ልዑክ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ጫላ ሆርዶፋ (ዶ/ር) ከብሪታኒያ አግሪ ቢዝነስ ትሬድ ሚሽን ልዑክ አባላት ጋር በግብርና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ባደረጉት ውይይት፤ በግብርናው ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
በዚህመ በምግብ ሰብል፣ በቅባት ሰብል፣ በጥራጥሬ እና በኢንዱስትሪ ሰብሎች፣ በእንስስሳት ሀብት ልማት፣ በግብርና ሜካናይዜሽን፣ በመስኖ ልማት፣ ለአፈር ለምነት የሚውል በኖራ ምርትና በተፈጥሮ ማዳበሪያ በኩል ሰፊ የኢንቨስትመንትና የገበያ አማራጮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ለእንስሳት ሀብት ልማት በተሰጠው ትኩረት ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው÷ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የስራ ዕድል በመፍጠር እና ኢኮኖሚን በማሳደግ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ያለውን ይህንን ዘርፍ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የግል ሴክተሮች እና ባለሀብቶች ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አስረድዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የውሃ ሀብት ለግብርና ኢንቨስትመንት ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው÷ ባለሀብቶችም መንግስት ለግብርና ኢንቨስትመንት ከሰጠው ማበረታቻ ጋር ይህንን ዕድል መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በወተት ሀብት ልማት፣ በዶሮ ልማት፣ በማር ልማት፣ በእንስሳት ጤና፣ በዘርና በእንስሳት መኖ ልማት ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በስፋት መምከራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው÷ የቀረበላቸውን አማራጮችን በመጠቀም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት ከሚኒስቴሩ ጋር ለመስራት እንደሚፈልጉ አረጋግጠዋል፡፡