ኢትዮጵያ የጀኔቫ ስምምነት መርሆችን ታከብራለች- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 1949 የተፈረመውን የጄኔቫ ስምምነት መርህ በአግባቡ እንደምታከብር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
አራቱ የጄኔቫ ስምምነቶች 75ኛ ዓመት መታሰቢያ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን÷ በዚሁ ወቅት ዓለም አቀፉ የሰብዓዊነት ሕግ ኮከስ ሥራ ጀምሯል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ተወካይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የጄኔቫ ስምምነቶች በትጥቅ ግጭቶች ጊዜ የሰውን ልጅ ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ የተደረሰ ስምምነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የጄኔቫ ጉባዔ መታሰቢያ የሰብዓዊ ሕጎች ዘመናትን ተሻግረው ተግባራዊ የሚደረጉበት ሌጋሲ መሆኑን ጠቅሰው÷ እነዚህ ስምምነቶች መከበር እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያም የጀኔቫ ስምምነት መርሆችን ለማክበር ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
አራቱ የጄኔቫ ስምምነቶች በተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት የጸደቁ እና በቀጣናዊ እንዲሁም በብሔራዊ ሕጎች ውስጥ የተካተቱ የሰብዓዊ ሕጎች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡