የተገባደደው ዓመት በፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል የታየበት ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተገባደደው 2016 ዓ.ም በፈተናዎች ውስጥ በማለፍ በርካታ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ተናገሩ፤
ርዕሰ መስተዳድሩ ለአዲስ ዓመት ባስተላፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ በእቅድ እና ጠንክሮ በመስራት ሀገራዊ ትልሞችን በፈተናዎች ውስጥም ሆኖ ማሳካት ይቻላል ብለዋል፡፡
ለዚህም የተገባደደው የ2016 ዓመት ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችና ድሎች ማሳያ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
በዓመቱ በመላ ሀገሪቱ በተሰሩ ስራዎች ውጤት መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በግብርና መስክ የታየው ውጤት አመርቂ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ግብርናን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።
ግብርናን በማዘመንና በትኩረት በመስራት በምግብ እራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ሊሳካ እንደሚችል በተግባር የታየ መሆኑን ገልዋል።
ከዚህ ባለፈም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመንገድ፣ የትምህርት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በተሰራው ስራ ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ በ2017 የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡና መንግስት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በ2017 የክልሉ ህዝብ እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊያን ለበለጠ ስኬት በአንድነት መስራት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡