አዳዲስ አስተሳሰቦችንና የልማት ውጥኖችን በመያዝ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እንሰራለን – ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዳዲስ አስተሳሰቦችንና የልማት ውጥኖችን በመያዝ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እንሰራለን ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የአብሮነትና አንድነት ይበልጥ እንዲጎለብት እመኛለሁ ብለዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በርካታ ድሎችን በተለያዩ መስኮች ማስመዝገቧን አስታውሰው፤ ዓመቱ ትላልቅ ሀገራዊ ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ ስራዎች የተከናወኑበት፣ የሀብት ማፍራት ስራዎች የተሰሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።
ለመጪው ትውልድ አሻራ ያሳረፍንበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አብዛኛው ስራ የተጠናቀቀበትና ተጨማሪ ተርባይኖች ስራ የጀመሩበት ለህዝቡ ታላቅ ብስራት የተበሰረበት ዓመት እንደነበረም ጠቅሰዋል።
በክልላችንም ትላልቅ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው አስተዋጽኦ ያሏቸው ፕሮጀክቶች የተከናወኑበት፤ ዜጎች የኢኮኖሚ አቅም እንዲፈጥሩ ዕድል የሰጡ ናቸው ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሀገራዊ ኢኮኖሚን ከፍ ለማድረግና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ስራዎች የተከናወኑበት ዓመት መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የሰላምና ጸጥታ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በክልሉ በተሰራው ስራ ስራ አጥነትን የመቀነስ፣ የተረጋጋ የፖለቲካ አካባቢ የመፍጠርና የተጠናከረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች እንዲዳብሩ መሰራቱንም አብራርተዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ ወደ ልማት የተመለሰበት፣ በሌማት ትሩፋቶች የተሳፉበትና በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በአትክልትና ፍራፍሬ በስፋት የተሳተፉበት ዘመን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የማምረት አቅምን በማሳደግ የተሻለ ምርት የተገኘበት ገበያውን ለማረጋጋት ሰፊ ስራዎች የተሰራበት ዘመን እንደሆነ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል።
በ2017 በጀት ዓመት የተጀመሩ መልካም ስራዎችን በማጠናከር አዳዲስ አስተሳሰቦችን እና የልማት ውጥኖችን በመያዝ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በመንገድ፣ በትምህርት፣ በጤናና መሰል ስራዎች የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአዲሱ ዓመት የተቸገሩትን በመርዳትና ማዕድ በማጋራት ይበልጥ አንድነትን በማጠናከር አዲሱን ዓመት መቀበልና ማክበር ይገባናል በማለት ገልጸው፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተሳሰብ ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።