Fana: At a Speed of Life!

ኤሎን መስክ እስከ ፈረንጆቹ 2027 የመጀመሪያው ትሪሊየነር ሊሆን እንደሚችል ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካዊው የዓለም ቁጥር አንድ ባለሀብት ኤሎን መስክ እስከ ፈረንጆቹ 2027 የመጀመሪያው ትሪሊየነር ሊሆን እንደሚችል ግሎባል ኢዱኬሽን የተሰኘ የቢዝነስ ኩባንያ ሪፖርት አመላከተ፡፡

ሕንዳዊው ጓታም አዳኒ፣ አሜሪካዊው የኒቪዲያ ኩባንያ ባለቤት ጆንሰን ሁዋንግ እና ኢንዶኔዥያዊው ፕራጆጉ ፓንጊስቶ ከኤሎን መስክ ጋር ትሪሊየነር ለመሆን እንደሚፎካከሩም ተጠቁሟል፡፡

ሦስት ባለሀብቶች እስከ 2028 ሀብታቸው 1 ትሪሊየን ዶላር እንደሚደርስ ያመላከተው ሪፖርቱ÷ ኤሎን መስክ አንድ ዓመት ቀድሞ የመጀመሪው ትሪሊየነር የሚሆንበት ዕድል እንዳለ ጠቅሷል፡፡

የቴስላ ኩባንያ እና “ኤክስ” ባለቤት ኤሎን መስክ አማካኝ ዓመታዊ የሀብት መጠን ዕድገት 109 ነጥብ 88 በመቶ ሲሆን÷ አጠቃላይ ሀብቱም 237 ቢሊየን ዶላር መድረሱ ተገልጿል፡፡

የቴስላ ኩባንያ የሚያመርታቸው የኤሌክትሪክ መኪናዎች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያላቸው ተቀባይነት ለግለሰቡ ፈጣን የሀብት መጠን ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ተብሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2012 ኤሎን መስክ 2 ቢሊየን ዶላር ሀብት በማስመዝገብ በፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ መካተቱ የሚታወስ ሲሆን÷ በ2021 የአማዞን መስራቹን ጄፍ ቤዞስ በመብለጥ የዓለም ቁጥር አንድ ባለሀብት መሆን ችሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.