የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዛሬም ቁርጠኛና ዝግጁ ነን – የመከላከያና የፖሊስ አባላት
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነት በተቀናጀ አግባብ በአስተማማኝነት ለመጠበቅ ዛሬም ቁርጠኛና ዝግጁ መሆናቸውን የመከላከያና የፖሊስ አባላት ገለጹ።
“ህብር ለሁለተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ የጳጉሜን 3 ሉዓላዊነት ቀን የሀገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ጨምሮ ሌሎችም የሰላም አስከባሪ አባላት በተገኙበት እየተከበረ ነው፡፡
በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ምስራቅ ዕዝ 801ኛ ኮር ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ሻለቃ መላኩ ቶላ እንደገለጹት÷ ሰራዊቱ የሀገርና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ከህዝብ ጋር እየሰራ ይገኛል።
”እስከ ሕይወት መስዋት በመክፈል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለመጠበቅ ዛሬም ቁርጠኛና ዝግጁ ነን” ሲሉም አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡም አንድነቱን ጠብቆ ከጎናችን መሰለፉ የበለጠ ጀግንነት እንድንላበስ አደርጎናል ያሉት ሻለቃ መላኩ÷ዛሬ የሉዓላዊነት ቀንን በጋራ ማክበር መቻሉም ለተሻለ ግዳጅ አፈፃፀም የበለጠ ተነሳሽነትን የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።
በፌዴራል ፖሊስ የሰሜን ምስራቅ መምሪያ ሪጅመንት አንድ አባል ረዳት ሳጅን ማሙሽ ዱሬ በበኩላቸው÷የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብሮ ለማስቀጠል ማንኛውንም መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ ገልጸዋል።
በቀጣይም የሚሰጣቸውን የትኛውንም ግዳጅ በብቃት በመወጣት ሀገርና ህዝዝብ ለመጠበቅ ዝግጁ እንደሆኑ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡