ሉዓላዊነት በደምና በላብ የሚጠበቅ ዕሴት ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሉዓላዊነት በደምና በላብ የሚጠበቅ ነው ዕሴት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
በሳይንስ ሙዚዬም የሉዓላዊነት ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ንግግር ያደረጉት ም/ጠ/ሚ ተመስገን ÷ሉዓላዊነት በደምም፤ በላብም የሚጠበቅ ዕሴት መሆኑን አውስተዋል፡፡
የሀገር ነፃነትና ዳርድንበር እንዲሁም የወገንን ክብር ማስጠበቅ የሚቻለው በደም መስዋዕትነት ነው ብለዋል።
የፖሊሲ፣የኢኮኖሚ፣የእውቀት፣የቴክኖሎጂ እና የበጀት ሉዓላዊነትን ማስከበር የሚቻለው ደግሞ በላብ አማካኝነት መሆኑን ነው ያነሱት።
በመሆኑም ሁላችንም የሉዓላዊነታችን ጠባቂ ነንና ጊዜያችንን እውቀታችንንና ጉልበታችንን ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት መጠቀም ይገባል ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ ሉዓላዊነቷ የተከበረች ሆና እንድትኖር ያለስስት ውድ ሕይወታቸውን የሰጡ፣ደማቸውን ያፈሰሱና አካላቸውን የገበሩ ጀግኖች ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ