ኢትዮጵያ የነገው ትውልድ ርስት ናትና ሉዓላዊነቷን አስከብረን እናኖራታለን – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የነገው ትውልድ ርስት ናትና ሉዓላዊነቷን አስከብረን እናኖራታለን ሲሉ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።
አቶ አደም ፋራህ ዛሬ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚከበረውን የሉዓላዊነት ቀን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ነው ይህንን ያሉት፡፡
በመልዕክታቸውም ፥ አጥንታችንን ከስክሰን፣ ደማችንን አፍስሰን በዱር በገደሉ በቁር በሐሩሩ ኢትዮጵያን ብለን የተዋደቅነው ለሉዓላዊነቷ ባለን ቁርጠኝነት ብሎም ታፍራ ለመኖሯ ባለን ተቆርቋሪነት ነው ብለዋል።
ሉዓላዊነቷ ለእድገቷ ደምስር፣ ለዜጎቿ ማንነታዊ ትስስር መሆኑን የተረዱ ጀግኖች በተለያዩ ቦታዎች ስለ ኢትዮጵያ መዋደቃቸውንም ነው የተናገሩት።
ግዛታዊ አንድነታችንን፣ ሀገራዊ ክብራችንን በደማችን አስከብረው የኢትዮጵያን ክብር በታላቅ ግርማ እና ሞገስ አይደፈሬ ሆኖ እንዲኖር ያደረጉ እልፍ አእላፍ ጀግኖች ከኢትዮጵያ ማህፀን ፈልቀዋል ሲሉም ገልጸዋል።
ዛሬ የተረከብናት ኢትዮጵያ የትላንት ጀግኖች ቅርስ፣ የዛሬ ባለ አደራዎች ውርስ፣ የነገው ትውልድ ርስት ናትና ሉዓላዊነቷን አስከብረን እናኖራታለንም ነው ያሉት።
ድህነትን ድል በመንሳት፣ ሀገራዊ አንድነታችንን አጠናክረን በጋራ በመቆም እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ የሚሆን ሀብት በመፍጠር በደም ያስከበርነውን ሉዓላዊነት በላባችን ሁለንተናዊነቱን አረጋግጠን እናፀናዋለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።