Fana: At a Speed of Life!

ሠራዊቱ የተስፋፊዎችን የጦርነት ነጋሪት ጉሸማ ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል – ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ሠራዊት የተስፋፊዎችን የጦርነት ነጋሪት ጉሸማ ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በ47ኛው የምስራቅ ዕዝ ምስረታ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የዕዙን የምስረታ በዓል ከሰላም ወዳዱ የሶማሌ ህዝብና ከጀግናው የዕዙ አመራርና አባላት ጋር ለማክበር በመቻሌ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡

ዕዙ ከምስረታው ማግስት ጀምሮም ተስፋፊውን የዚያድ ባሬ ጦር ጨምሮ የተለያዩ የሽብር ሀይሎችን በመከላከልና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰጠውን ግዳጅ በጀግንነት ሲመክት የቆየ አንጋፋና ጀግና ዕዝ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ዕዙ የዚያድ ባሬ ጦር ወደ መሀል ሀገር ያደረገውን ወረራ መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የሀገሩን ዳር ድንበር እንዳስከበረ አስታውሰዋል።

ዕዙ የሀገር ሰላም፣ ሉዓላዊነትና አንድነትን በማስጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉና የሰራዊቱ መመኪያ መሆኑን ገልጸው፤ ሠራዊቱ ሀገርን ለመውረር የሞከሩ ሀይሎች ለመመከት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለመውረር ግፊት ሲያደርጉና ግጭት ሲያባብሱ የነበሩ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች አብረው የቆሙ ቢመስሉም በሽንፈት ጊዜ እንደማይገኙ ከታሪክ መማር ይገባል ብለዋል፡፡

ሠራዊቱ በቀጠናው ያለውን የተስፋፊዎች የጦርነት ነጋሪት ጉሸማ ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት ፊልድ ማርሻሉ፡፡

ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም ሀገርን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ከሞከሩ ዳግመኛ እንዳያስቡት አድርጎ ለመመከት የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ለሠራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.