በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በድብቅ የሚፈጸሙ መሆናቸው የፍርድ ሒደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ሰዎች በሌሉባቸው ቦታዎች እና ጊዜያት የሚፈጸሙ መሆናቸው የፍርድ ሒደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተመላከተ፡፡
የሴቶችና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በሴቶች እና ሕጻናት መብት አያያዝ ዙሪያ ከአማራ ክልል ዳኞች እና የጉባዔ ተሿሚዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መነሻቸው የተዛባ የሥርዓተ ጾታ አመለካከት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የሴቶችና ሕጻናትን መብትና የፍትሕ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ ገና ረጅም ጉዞ የሚጠይቅ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ጾታዊ ጥቃት የሀገር ተረካቢ ሕጻናትን መፃዒ ተስፋ በማጨለም ገና በማለዳው ተሰናክለው እርምጃቸው እንዲገታ እያደረገ እንደሚገኝም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ከፍርድ ቤቶች እና ሌሎች የፍትህ አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ፍርድ ቤት ዳኞች በበኩላቸው ÷በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ሰዎች በሌሉባቸው ቦታዎች እና ጊዜያት የሚፈጸሙ መሆናቸው የፍርድ ሒደቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል።
በመድረኩ በሕጻናትና በሴቶች መብት ዙሪያ እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል መሻሻል አለባቸው የተባሉ የሕግ እና አፈፃፀም ጉዳዮች መኖራቸው ተነስተው በስፋት ውይይት እንደተደረገባቸው የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡