የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው የወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና ላይ እንዲያተኩሩ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁሉም የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው የወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አሳሰበ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቴ በወባ በሽታ መከላከል ሣምንት ማስጀመሪያ ላይ በክልሉ የወባ በሽታ ሥርጭት አለመገታቱን ገልጸው÷ እስከ አሁንም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ብለዋል፡፡
ማኅበረሰቡን በማስተባበር የወባ መራቢያ ቦታዎችን ማጽዳትና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ለማከናወን ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው የወባ በሽታ ምርመራና ሕክምና ላይ እንዲያተኩሩም አሳስበዋል።
ከመስከረም እስከ ታኅሣስ ሊፈጠር የሚችለውን የወባ ሥርጭት ለመግታት የቤት ውስጥ የፀረ-ወባ ኬሚኬል ርጭት ለማካሄድ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የወባ በሽታን ለመከላከልና መቆጣጠር ግብረ-ኃይል አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን የገለጹት የግብረ-ኃይሉ ሰብሳቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)÷ የግብዓት እጥረቶችን መፍታትና ማኅበረሰቡን ማንቃት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ