የምስራቅ ዕዝ የሶማሌ ክልል የፀጥታ ሃይሎችን አቅም በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምስራቅ ዕዝ የሶማሌ ክልል የፀጥታ ሃይሎችን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን የክልሉ የፀጥታ ሃይል አመራሮች ተናግረዋል፡፡
የሶማሌ ክልል የፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ደይብ አህመድ÷ የመከላከያ ሠራዊት በተለይ ደግሞ የምስራቅ ዕዝ በክልሉ ሰላም እና ፀጥታ በተሟላ ሁኔታ እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈሉን ተናግረዋል፡፡
ዕዙ የሶማሌ ክልልን የፀጥታ ሃይሎች በወታደራዊ፣ስነ-ልቦናዊ፣ አካላዊ እና በስነ-ምግባር በማሰልጠን የክልሉን ብቻ ሳይሆን የቀጣናውን ጨምሮ የሀገርን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ እንዲችሉ ማድረጉንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አብዲ አሊ በበኩላቸው÷ የክልሉ ፖሊስ ጀግንነትን ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወርሷል ሲሉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የፌስቡክ ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የምስራቅ ዕዝ የ47ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ከሰራዊቱ ጋር ለማክበር ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል፡፡