Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዲሱን የተማሪዎች ቅበላ አሰራር ከ2017 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዲሱን የተማሪዎች ቅበላ አሰራርን ከ2017 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

አሰራሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ማስተማሪያ ተቋም ያደርገዋል ተብሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) አዲሱን አሰራር አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ አዲሱ የተማሪዎች ቅበላ አሰራር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሙሉ ራስ-ገዝነት የሚያደርገው የሽግግር ሂደት አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡

አሰራሩ የሚተገበረው በመጪው የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው አዲስ የቅድመ ምረቃ እና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ጀምሮ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች የተዘጋጀውን የመወዳደሪያ ነጥብ፣ የመግቢያ ፈተና እንዲሁም ሌሎች መስፈርቶችን ሲያሟሉ ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደሚገቡ ተናግረዋል።

አሰራሩ በመንግስት ወጪ የሚሸፈን የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እና በግል ወጪን በመሸፈን የተማሪዎችን ስብጥር በጠበቀ መልኩ ማስተናገድ እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ መሆኑም ተገልጿል፡፡

አዲሱ የተማሪዎች ቅበላ ስርዓት ለቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች በፖሊሲው እና በመመሪያው መሰረት የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡

ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ከታዳጊ ክልል ለሚመጡ ተማሪዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ፍትሓዊነቱ ይረጋገጣልም መባሉን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በ2014፣ 2015 እና 2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ወስደው የማለፊያ ነጥብ ያገኙ ተማሪዎች የሚወጣውን መስፈርት ታሳቢ አድርገው በዩኒቨርሲቲው ፖርታል https://portal.aau.edu.et መመዝገብ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.