በህገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው አብድል ራህማን ሚላድ ሊቢያ ውስጥ ተገደለ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ -ወጥ ሰዎች ዝውውር ወንጀል በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው አብድል ራህማን ሚላድ በትላንትናው እለት ሊቢያ ውስጥ መገደሉ ተሰምቷል፡፡
ግለሰቡ በምዕራባዊ ሊቢያ በምትገኘው ዛውያ ከተማ የራሱን ታጣቂ ቡድን በማቋቋም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በተደራጀ መልኩ ሲያካሂድ ነበር ተብሏል፡፡
በግለሰቡ የተቋቋሙት ታጣቂ ቡድኖች በባህር ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት ፍልሰተኞችን አሳፍረው ሲጓዙ የነበሩ ጀልባዎች እንዲሰጥሙ እና ሰዎች ህይወታቸው በባህር ላይ እንዲያልፉ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ስደተኞችን በማገት በርካታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ሲፈፅም እና ሲያስፈጽም እንደነበር ነው የተገለፀው፡፡
በዚህ የወንጀል ድርጊቱም በግለሰቡ እና በሌሎች አምስት ግለሰቦች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ተጥሎባቸው እንደነበር ተገልጿል፡፡
ግለሰቡ በበርካታ ዓለም ዓቀፋዊ ተቋማት ሲፈለግ የነበረ ሲሆን በትናንትናው እለት ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ ማለፉን አረብ ኒውስ ዘግቧል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች በተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስልም አብድል ራህማን ሚላድ በምዕራባዊ ሊቢያ ሲያድ በተባለው አካባቢ ሲንቀሳቀስበት የነበረ መኪና በጥይት ተበሳስቶ ታይቷል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ከሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ ዲቤባህ መንግስት የተሰጠ አስተያየት አለመኖሩ የተገለፀ ሲሆን ምዕራባዊ ሊቢያን የሚያስተዳደረው ወታደራዊ ሀይል ግን ግለሰቡ ባልታወቁ ሰዎች መገደሉን አረጋግጧል፡፡
በነዳጅ ምርቷ የምትታወቀው ሊቢያ ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት በመነሳት ወደ አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞች ዋነኛ መተላለፊያ መሆኗ ይታወቃል።